አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሰላም ወዳዱ የቦረና እና ጉጂ ህዝብ ብንዘገይም ደርሰንለታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡
በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ቦረና የኦሮሞን ማንነት እና ባህል ጠብቆ ያቆየ እንዲሁም ከጉጂና ባሌ ኦሮሞዎች ጋር ሲተባበር የኖረ ታላቅ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡
ቦረና ከአዲስ አበባ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነውን እና አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን ገንብቶ በማጠናቀቁ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ብንዘገይም ለቦረና እና ጉጂ ህዝብ ደርሰናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒትሩ÷ በቀጣይም ልማት እንዲረጋገጥ ሰላም ወዳዱ የጉጂ ህዝብ በትብብር እንዲሰራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አስፈላጊ በሆኑ እና ጥናት በተደረገባቸው አካባቢዎች የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በደቡብ እና ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ገበያን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ