የሀገር ውስጥ ዜና

የቦረና ህዝብ ራሱን ከተረጂነት ነጻ አውጥቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

May 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዓመታት በድርቅ ሲጠቃ የነበረው የቦረና ህዝብ በራሱ ጥረት ራሱን ከእርዳታ አውጥቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት በምስራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ በኩታገጠም እየለማ የሚገኝ የስንዴ ሰብል በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የቦረና ህዝብ ከ2 ወይም 3 ዓመታት በፊት በውሃ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ድርቅ ሲከሰትበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም 90 በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ህዝብ በሴፍትኔት ሲታገዝ መቆየቱን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት አካባቢውን በማልማት የአካባቢውን መጥፎ ታሪክ ቀይሯል፤ ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ከሴፍቲኔት ወጥቷል ብለዋል፡፡

ዘንድሮ በሊበን ወረዳ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን ገልጸው፤ በቂ ውሃ ከተገኘ ከዚህም በላይ ሊለማ እንደሚችልም አመላክተዋል፡

ይህም ከራስ አቅም አልፎ ለገበያ ሊተርፍ የሚችል ምርት ሊያስገኝ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከትቂት ዓመታት በፊት ለእርዳታ የመጣንበት ቦታ አሁን በዚህ መልኩ ተቀይሮ ማየቴ እጅግ አስደስቶኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ለውጥ በሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰፊ ስራ ወዳድ ህዝብ መኖሩን ጠቅሰው፤ በርትቶ በመስራት ከልመና እና ከርሃብ መውጣት አለብን ነው ያሉት፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው