አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት እየሰራን ነው አለ የጎንደር ከተማና አካባቢው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፡፡
በጎንደር ከተማና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ መጪው ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራና በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቅማንት ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተገኙ ደረጀ ምርጫ ለአንድ ሀገር ህልውና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዴሞክራሲን መለማመድና የምርጫ ውጤትን በፀጋ መቀበል አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
በድምጽ መስጫ ወቅት ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካላት በጋራ መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ የአማራ ክልል አስተባባሪ መኮንን ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ሰላማዊ የትግል መስመርን መርጦ በምርጫ መወዳደሩን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ሀገርን ሊያሻግር የሚችል የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ያለውን ፓርቲ በነፃነት መምረጥ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የጎንደር ቅርንጫፍ ተወካይ የዝናወርቅ ታደለ ሰላማዊ ሀገር ለመገንባት የእያንዳንዱ ዜጋ ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁሉም ዜጋ ለሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ፋሲል ሰንደቁ÷ በምርጫ ምዝገባ ሂደት ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሳዩት ትብብርና ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራና በቅንጅት እየሰሩ ስለመሆናቸውም አስታውሰዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለሀገር ሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።
በግዛቸው ግርማዬ