ዓለምአቀፋዊ ዜና

በላኦስ በጎርፍ ምክንያት በተዘጋ ዋሻ ውስጥ የቆዩ 5 ሰዎች ከሳምንት በኋላ በህይወት ተገኙ

By Yonas Getnet

May 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምስራቅ እስያዊቷ ሀገር ላኦስ በጎርፍ ምክንያት በተዘጋ ዋሻ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያህል ተቀብረው የቆዩ 5 ሰዎች በህይወት ተገኝተዋል።

ባለፈው ሳምንት በላኦስ ዛይሶምቡን ግዛት በሚገኝ ዋሻ ውስጥ በአካባቢው በባህላዊ መንገድ የወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከ100 ሜትር በላይ ዘልቀው መግባታቸው ተገልጿል።

በወቅቱ ድንገት የጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ በማስከተሉ የዋሻውን መግቢያ ሙሉ በሙሉ እንደዘጋውና በዋሻው ውስጥ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ሦስቱ ሲያመልጡ ሰባቱ በዋሻው ውስጥ እንዳሉ እንደተዘጋባቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከዋሻው መዘጋት ያመለጡት ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ ጥቆማ በመስጠታቸው የነፍስ አድን ዘመቻ እንዲጀመር ማድረግ የቻሉ ሲሆን÷ በዚህም ምክንያት ከአንድ ሳምንት ፍለጋ በኋላ 5 ሰዎች በህይወት መገኘታቸው ተመላክቷል።

አምስቱ ሰዎች የጭቃው ጎርፍ ዋሻውን ሲሞላ ከፍ ባሉ አለቶች ላይ ተጠልለው ለአንድ ሳምንት ሙሉ አስከፊውን ሁኔታ በማለፍ በህይወት መገኘታቸውም ነው የተገለጸው።

የሀገሪቱ መንግሥት ወታደሮችን፣ ፖሊሶችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰማራት እጅግ በጣም ጠባብ እና አደገኛ በሆኑ የዋሻ መተላለፊያዎች ውስጥ አልፈው አምስቱን ሰዎች ማዳን እንደቻለም ተገልጿል።

አሁንም የቀሩ ሁለት ሰዎችን ለማዳን ፍለጋው እንደቀጠለ ዴይሊ ሜይል ዘግቧል።

በዮናስ ጌትነት