የሀገር ውስጥ ዜና

የቦረና ባሕል ማዕከል የሕዝቡን ባህል እና ታሪክ በመሰነድ ሚናው የጎላ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

May 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቦረና ባሕል ማዕከል የሕዝቡን ባህል እና ታሪክ በመሰነድ እና ለሌሎች በማስተማር ረገድ ሚናው የጎላ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በያቤሎ ከተማ የተገነባውን የቦረና ባሕል ማዕከል ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ ኦሮሞ ቦረና ታላቅ ነው ቢልም እውነታው ግን ቦረና የአፍሪካም የዓለምም ታላቅ ሕዝብ ነው።

አሜሪካ ዴሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግ ስትጀምር ቦረና 47ኛው አባ ገዳ ላይ ደርሶ እንደነበር አስታውሰው÷ በዚህም ለ300 ዓመታት የስራ ድርሻን ተከፋፍሎ ሲተዳደር የነበረ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን የዴሞክራሲ ጠንሳሽ እና ባለቤት አሜሪካ እንደሆነች ቢነገርም እውነታው ግን የዴሞክራሲ መስራች የቦረና ሕዝብ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ቦረና ያገኘውን ሁሉ ለእኔ የሚል ሕዝብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይልቁንም ያለውን በማካፈል የሚያምን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ ባህል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ማደግ እንዳለበት ጠቅሰው÷ በገዳ ሥርዓት መሰረት እኩልነት እና አንድነት የሰፈነባት ሀገር እስክትሆን ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የባህል ማዕከሉ ምርቃት የቦረናን ሕዝብ ባህል እና ታሪክ በመሰነድ እና ለሌሎች በማስተማር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን በማንሳት እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአቤል ነዋይ