አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚበሰርበት ነው አሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ።
አቶ ሰለሞን አየለ እንዳሉት÷ ምክር ቤቱ ከ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት እየሰራ ነው።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና የዲጂታል ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት በስኬት ማጠናቀቅ እንደተቻለ ገልጸው÷ በዚህም የምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ የአየር ሰዓት የፖሊሲ አማራጭ ማቀረባቸውን አመልክተዋል።
በተለያዩ አካላት በተዘጋጁ የክርክር መድረኮች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በፍትሐዊነት ለሕዝብ ሐሳባቸውን ማስተዋወቅ መቻላቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ተከታታይ ኮሚቴ በማቋቋም ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ለጠቅላላ ምርጫ ሂደቱ አስቻይ ሁኔታዎችን ለማጥናትና ለመለየት ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።
ይህ የምርጫ ጉዳዮችን የሚከታተል ዴስክ አጠቃላይ ሁኔታዎችን በመገምገም ስኬታማ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን በቅርበት መከታተሉንም አስታውቀዋል።
ከግንቦት 20 ጀምሮ የጥሞና ጊዜ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ሕጉ ተገዢ በመሆን ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት በአርዓያነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት መሆኑን ገልጸው÷ መራጩ ሕዝብ እንደተለመደው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።