አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት 5 አመታት የልማት አብዮት አካሂዳለች አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በባለፉት 10 ቀናት ብቻ 11 ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።
ለአብነትም ፦
1. በኢንዱስትሪ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ይህ ፓርክ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።
2. የማህበራዊ ልማት (የመኖሪያ ቤቶች)፤ ሶስቱ የበጎነት መንደሮችን በአዲስ ከተማ፣ በኮልፌ ቀራንዮ እና የካ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የመኖርያ ቤቶች ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለአቅመ ደካማዎች እና ለአካል ጉዳተኞች የማስተላለፍ ስራ ተሰርቷል፡፡
3. የመዝናኛ እና የህዝብ ፓርኮች ፤በአዲስ ከተማ (አስኮ አዲስ ሰፈር) በ30 ሺህ ካሬ ሜትር እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ18 ሄክታር ቦታ ላይ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻ እና የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ተመርቀዋል። እነዚህ ማዕከላት ህፃናትን፣ ወጣቶችን እና አረጋውያንን ያካተቱ፣ ማህበረሰቡ በጋራ የሚጠቀምባቸው ናቸው።
4. የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የግብይት ማዕከላትን የማስፋት ስራ አካል የሆነው 7ኛው የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል፣ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
5. ዘመናዊ የገበያና የትራንስፖርት ማዕከል፤ አይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የአድዋ የገበያ ማዕከል እና ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናል ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። የዚህ ማዕከል ሱቆች እና ካፍቴሪያዎች ለፒያሳ ልማት ተነሺዎች በዕጣ ተላልፈዋል።
6. በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ3 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ፣ 16 ሱቆችን እና 18 ሼዶችን የያዘ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ማዕከል አገልግሎት ክፍት ተደርጓል ።
7. የስፖርት እና የወጣቶች ማዕከል፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የለሚ ኮሚኒቲ ስታዲየም፣ 5 ስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ 95 የህፃናት መጫወቻዎች፣ 6 የህፃናት ማቆያ (Daycare) ማዕከላት፣ ካፍቴሪያዎች እና አምፊ ቲያትሮችን ጨምሮ ለወጣቶች ተጠቃሚነት የሚያገለግሉ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
8. በልደታ ክ/ከተማ ለትውልድ ግንባታ መሰረት የሚጥሉ ሁለት ት/ቤቶች እና ሶስት የህፃናት ማቆያ ማእከል ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደረገዋል ።
9. የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከላት ተጠቃሚዎች ለነበሩ 400 ነዋሪዎቻችን መነሻ ካፒታልና የመስሪያ ቁሳቁስ በማሟሟላት ከተረጂነት ወደ የስራ እድል ተጠቃሚነት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።
10. 7ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በላፍቶ ክፍለ ከተማ ተመርቋል።
11. ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነው፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ የተደገፈው እና እጅግ ዘመናዊ የሆነው የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለምርቃት በቅቷል።
አንዳንዶች እነዚህ ፕሮጀክቶች ለምርጫ ተብሎ እንደተከናወነ ያነሳሉ ያሉት ከንቲባዋ፤ ነገር ግን እውነታው ቀድሞ ያልተሰራ ለምርጫም ሊደርስ አይችልም፤ ተሰርቶም ለምርጫ ከዋለ ዋናው ህዝቡና ሀገር ተጠቃሚ ይሁን እንጂ ችግር የለውም ብለዋል፡፡