አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ2018/19 የመኸር እርሻ በቂ ምርጥ ዘር አቅርቤያለሁ አለ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ።
የኢንተርፕራይዙ ባሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሙሉቀን አስቻለው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት÷ ለመኸር እርሻ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በጥራት በማምረት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ይገኛል።
አሁን ላይ ከ450 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር መዘጋጀቱን ገልጸው÷ ከዚህ ወስጥ 150 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር በመጋዘን ማስገባታቸውን ተናግረዋል።
ኢንተርፕራይዙ እንደ ሀገር በ32 ሺህ ሄክታር ላይ ከሚያከናውነው የዘር ብዜት ውስጥ 17 ሺህ 700 ሄክታሩ በባሌ ዞን የሚለማ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር በምግብ እራስን ለመቻል የተያዘውን ውጥን ለማሳካት በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር ኢንተርፕራይዙ በትኩረት እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በታሪኩ ለገሠ