የሀገር ውስጥ ዜና

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የበኩላችንን ለማበርከት ተዘጋጅተናል – የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች

By Mikias Ayele

May 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመምረጥ መብታቸውን በመጠቀም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅተናል አሉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በምርጫ ካርዳቸው ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል ለሚሉት አካል ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

መምህር ፍቃዱ ቶማስ÷ በጠቅላላ ምርጫው ሀገርና ሕዝብን ያሻግራል ብለው ለሚያምኑበት ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በምርጫው የሚወክላቸውን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የአንድ ሰው ድምፅ ትልቅ ዋጋ እንዳለው የጠቀሱት አቶ አብድራህማን ጅላሉ በበኩላቸው፤ የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ዙርያሽ ቶፊቅ በበኩላቸው፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያምኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።