አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ እየተሰራጨ ነው አለ በክልሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አብርሃም አንጁሎ በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁስን የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው የዝግጅት ሥራዎች በተደራጀ መልኩ ሲከናወን መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት በምርጫ ቦርድ መርሐ ግብር መሰረት የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እየተሰራጨ ያለው ቁሳቁስ በክልሉ ባሉ 56 የምርጫ ክልሎች ስር ወደሚገኙ 3 ሺህ 941 የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን አስታውቀዋል።
በወላይታ ዞን የሶዶ ዙሪያ-2 ምርጫ ክልል አስተባባሪ ምህረቱ ጋዴቦ በበኩላቸው÷ በምርጫ ክልሉ ሥር ለተደራጁ 108 የምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁስ የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የቁሳቁስ ስርጭቱ ደህንነቱ በተጠበቀና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።