የሀገር ውስጥ ዜና

የድምፅ መስጫ ወረቀት…

By Melaku Gedif

May 30, 2026

1. ለመራጩ ለምርጫ ጣቢያው ከተዘጋጀው የድምፅ መስጫ ወረቀት ለአንድ ምክር ቤት አንድ የድምፅ መስጫ ወረቀት በድምፅ መስጫ ወረቀት አዳዩ አማካይነት ይሰጠዋል።

2. በዕለቱ የሚካሄደው ምርጫ ከአንድ በላይ ለሆኑ ምክር ቤቶች ሲሆን÷  ለየምክር ቤቱ ምርጫ አንድ አንድ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ይሰጠዋል፡፡

3. የድምፅ መስጫ ወረቀት አዳይ የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ከጥራዙ ላይ በመነጠል ለየምክር ቤቱ የተዘጋጀውን የድምፅ መስጫ ወረቀት በጀርባው ላይ ማህተም በማድረግ ለመራጩ በመስጠት የትኛውን የድምጽ መስጫ ወረቀት የትኛው ሣጥን ውስጥ መክተት እንዳለበት ገለልተኛ በሆነ አኳኋን ያስረዳል፡፡

4. የድምፅ መስጫ ወረቀቱን የተቀበለ መራጭ ለዚሁ በተዘጋጀው ከማንም እይታ በተከለለው የምስጢር ቦታ በመግባት በሚስጥር ድምፅ ይሰጣል።

5. ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መራጮች ከመረጧቸው ሰዎች ጋር ወደ ምስጢር ክፍል በመግባት ድምፅ ይሰጣሉ።

6. ከላይ ከተገለጸው አግባብ ውጪ መራጩ ወደ ምስጢር ድምፅ መስጫው ገብቶ ድምፅ በመስጠት ላይ እያለ ማንም ሰው በምንም ሁኔታ ተከትሎ ወይም ተደርቦ መግባት ወይም ወደ ሚስጥራዊው ቦታ መጠጋት አይችልም።

7. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ እና በቦርዱ ፈቃድ የተሰጣቸው የእጩ ወኪሎችና ታዛቢዎች የምስጢር ድምፅ መስጫ ቦታ ላይ የተቀመጡ እስክሪብቶ እና መርገጫዎች በተገቢው ሁኔታ መኖራቸውን እና ሌሎች የተከለከሉ የቅስቀሳ ጽሑፎች አለመለጠፋቸውን ወይም አለመቀመጣቸውን መራጮች ድምፅ በማይሰጡበት ክፍተት በየተወሰነ ጊዜ እየገቡ ያረጋግጣሉ፡፡

8. መራጩ በአግባቡ ድምፅ የሰጠበትን የድምፅ መስጫ ወረቀት በቁመቱ ወደ ውስጥ በማጠፍ በምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የእጩ ወኪሎች ፣ እንዲሁም በታዛቢዎች ፊት ለፊት በቅርብ ዕይታ በግልፅ ስፍራ በተቀመጠው የድምፅ መስጫ ሳጥን ውስጥ በመክተት ከምርጫ ጣቢያው ይወጣል፡፡

9. በምርጫ ጣቢያው የተመደበው የድምፅ መስጫ ሣጥን ተቆጣጣሪ መራጮች የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን መራጮች በትክክለኛው የድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ ወረቀቱን መክተታቸውንና ከጣቢያው ይዘው አለመውጣታቸውን በመከታተል ያረጋግጣል፡፡

10. መራጩ የተሰጠውን የድምፅ መስጫ ወረቀት በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቶ የተበላሸበት እንደሆነ ሁኔታውን ለድምፅ መስጫ ወረቀት አዳይ በማስረዳት ሌላ የድምፅ መስጫ ወረቀት እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል፡፡

11. የድምፅ መስጫ ወረቀት አዳዩም የተጠቀሰውን የተበላሸ የድምፅ መስጫ ወረቀት የፊት ገጽ ሳይመለከት እንዲመለስ በማድረግ በጀርባው ላይ «የተበላሸ» የሚል ምልክት አድርጎ የተበላሸውን የድምፅ መስጫ ወረቀት ለዚሁ ተግባርና የምርጫ ዓይነት በተዘጋጀው “የተበላሹ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች” ፖስታ/ኤንቨሎፕ ውስጥ ይከታል፡፡