አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና የምርጫ ስርዓትን ለማጠናከር የአፍሪካ ሀገራት አንዳቸው ከሌላቸው ልምድ መቅሰም አለባቸው አሉ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት እና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ፡፡
ነገ የሚካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ አዲስ አበባ የሚገኙት ኡሁሩ ኬንያታ እንዳሉት፤ በአፍሪካ ህብረት ስር የተካሄዱ ምርጫን የመታዘብ ተግባራት የምርጫ ሂደቶችን ከመከታተል ያለፈ አስተዋጽኦ አላቸው።
ምርጫ የመታዘብ ተግባራቱ በአባል ሀገራቱ መካከል የልምድ ልውውጥና መልካም ተሞክሮዎችን በመቅሰም ዴሞክራሲያዊ ልማትን ለማስፈን ጭምር የተነደፉ ናቸው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የዴሞክራሲ ስርዓትን የበለጠ ለማጎልበት እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል የአቻ ለአቻ ትምህርትን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት አካል በመሆኑ በአህጉሪቱ በሚደረጉ ምርጫዎች በታዛቢነት እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።
የምርጫ ታዛቢነት ተልዕኮዎች እና ሌሎች የአፍሪካ ህብረት አሰራሮች ሀገራት ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ስኬታማ አካሄዶችን እንዲለዩ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ትምህርቶችን እንዲለማመዱ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሀገራት በሌሎች አህጉራት/አካባቢዎች የተዘጋጁ የአስተዳደር ስልቶችን ለመተግበር በአህጉሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ልምድ የተደገፈ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የተሞክሮ ልውውጥ በአህጉሪቱ ልዩ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ አውድ ውስጥ ያሉትን ጉዳዮች የሚፈቱ ሀገር በቀል ዴሞክራሲዊ ልምምዶችን ያመጣል ብለዋል፡፡
አፍሪካዊያን መር የሆነ ዴሞክራሲን የማጠናከር አካሄድ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” ለሚለው መርህ ማዕከል ሆኖ እንደሚቀጥል አፅንዖት ሰጥተዋል።