አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “በማለዳ ወጥቼ ድምጽ የሰጠሁት ለሀገሬና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገር ስለምመኝ ነው” አሉ የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ፍቃዱ መኮንን።
በማለዳ በሄርማታ መዋዕለ ሕፃናት ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፃቸውን የሰጡት የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ፍቃዱ፤ “ድምፄ ዋጋ እንዳለው ስለማውቅ በማለዳ 11 ሰዓት ላይ ከቤት ወጥቼ ተገኝቻለሁ”ብለዋል።
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እጅግ የተሳለጠና ጥሩ የነበረ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ “በዚህ ዕድሜዬ በማለዳ ወጥቼ ድምጽ የሰጠሁት ለአገሬና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገር ስለምመኝ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አሚዳ አባ ሉሌሳ በበኩላቸው፤ አካል ጉዳተኝነት ድምፅ ከመስጠት እንዳልከለከላቸው ገልጸዋል።
በምርጫ ጣቢያው ሲደርሱ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ድምፃቸውን መስጠታቸውን የገለጹት ወይዘሮ አሚዳ፤ ሂደቱ እጅግ ሰላማዊ እንደነበርና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የምርጫን አስፈላጊነት በመረዳት ድምፃቸውን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በቦሳ ኪቶ ፈያ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ የሰጡት ወይዘሮ ዓለሚቱ ከበደ እና አቶ ሲሳይ ዲጋ “የዛሬው ዕለት እስኪደርስ በጉጉት ስንጠብቅ ነበር” ብለዋል።