የሀገር ውስጥ ዜና

የዘንድሮ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን በድምጽ ካርድ ለመምረጥ ያለውን ፍላጎትና ጉጉት የሚያሳይ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

By Adimasu Aragawu

June 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን በድምጽ ካርድ ለመምረጥ ያለውን ፍላጎትና ጉጉት የሚያሳይ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።

ፕሬዚዳንት ታዬ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምጻቸውን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት÷ ከ54 ሚሊየን በላይ ሕዝብ መመዝገብ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን በድምጽ ካርድ ለመምረጥ ያለውን ፍላጎትና ጉጉት የሚያሳይ ነው።

በዚሁም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች መወዳደራቸውን አንስተው÷ ይህ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት በቀናና በበጎ መንገድ እየተጓዘና በውድድር ድምጽ በመስጠት የመታመንን ሂደት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

እኔ ዛሬ የምመርጠው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ድምጼን ለመጠቀም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ የመረጥኩት ለሀገሬ፣ ለማሕበረሰብና ለራሴ እንደ ግለሰብ ነው፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

መንግሥት የሚመረጠው በድምጽ ነው የሚለው ምልክት የምታይበት ወቅት ነው በማለትም ገልጸዋል።

ዛሬ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ እግር ስር ላይ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ÷ ይህ መለመድ ያለበት እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓትና ግንባታ በዚህ መልኩ መካሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአድማሱ አራጋው

#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያእየመረጠችነው #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision