የሀገር ውስጥ ዜና

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መምረጥ የቻሉት አካል ጉዳተኛ …

By abel neway

June 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ምክንያት እስካሁን መምረጥ ባልችልም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በመምረጤ ደስተኛ ነኝ አሉ ወ/ሮ ደስታ ደምሴ፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሲና ከተማ አስተዳደር ነዋሪዋ፤ የእግር ጉዳት ያለባቸውና በእጃቸው የሚሄዱ ናቸው ።

ባለፉት አምስት ምርጫዎች መምረጥ የምችልበት ዕድሜ ላይ የነበርኩ ቢሆንም ለመምረጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስላልነበረኝ ባለመሳተፌ እቆጭ ነበር ብለዋል።

በምኖርበት አካባቢ በነበረ የመሰረተ ልማት ችግር እና እኔም ለአካል ጉዳቴ የሰጠሁት የተሳሳተ አመለካከት እስካሁን በምርጫ መሳተፍ አልቻልኩም ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመምረጥ የሚያስችለኝን ካርድ ከወሰድኩ ጀምሮ ይህንን የምርጫ ቀን በጉጉት ስጠብቅ ነበር ያሉት ወ/ሮ ደስታ፤ ዛሬ ማለዳ ድምፄን በመስጠቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ነው ያሉት።

አሁን በታሪኬ ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጥኩት መንግሥት ልገለገል መሆኑን ሳስብ ኩራት ይሰማኛል በማለት ገልጸው፤ አንድ ድምፅ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የመራጭነት ካርድ የያዙ ዜጎች ድምፃቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በቀጣይ የመረጡት መንግሥት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆንባትን ኢትዮጵያን ዕውን እንዲያደርግ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

በደብረሲና የምርጫ ክልል ባሉ የምርጫ ጣቢያዎችም ከማለዳ ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፃቸውን እየሰጡ ነው።

በአበበ የሸዋልዑል