የሀገር ውስጥ ዜና

በአረካ ከተማ ማልደው ድምፅ የሰጡ አዛውንቶች …

By Yonas Getnet

June 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረካ ከተማ አዛውንቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዕድሜና የእርጅና ሕመም ሳይበግራቸው በማለዳ በመገኘት ድምፃቸውን በመስጠት አርአያ የሚሆን ተግባር አሳይተዋል።

በአረካ ከተማ ነዋሪና የዕድሜ ዘመን የልብ ጓደኛማቾች የሆኑት አዛውንቶቹ አቶ ሰለሞን ሳና እና አቶ ዳንኤል አላጎ ዛሬ ጠዋት ማልደው በመነሳት በቦሎሶ ሶሬ 3 ምርጫ ክልል አራዳ አጠና ምርጫ ጣቢያ በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

እነዚህ ሁለት አባቶች በሕይወት ዘመናቸው በርካታ ታሪኮችንና የመንግሥታት መፈራረቅን ያዩ፣ በኖሩበት ከተማም የተጣላን በማስታረቅና የተራራቀን በማቀራረብ የሚታወቁ ናቸው።

አዛውንቶቹ ከእርጅናና ከሕመም ጋር እየታገሉ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ሀገርን ይመራል ለሚሉት ፓርቲ ድምጽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላኛዋ አዛውንት ወ/ሮ ጎዚቴ ሙንጃራ ዕድሜ ሳይበግራቸው በማለዳ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል።

ወ/ሮ ጎዚቴ በሰጡት አስተያየት፣ ተወልደው ባረጁበት ከተማ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው የምትበጅ ሀገር ለማቆየት ሲሉ ድምፃቸውን መሥጠታቸውን ተናግረዋል።

በማስተዋል አሰፋ

#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያእየመረጠችነው #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision