አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተካሄደ የሚገኘውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ የተሰማሩ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን በቅርበት እየተመለከቱ ነው።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን በአዲስ አበባ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን እየጎበኙ ይገኛል። በተጨማሪም ቡድኑ በዛሬው ዕለት በህብረት ለምርጫ የተሰኘውን የሲቪል ማህበራት የምርጫ ትዝብት መረጃ መሰብሰቢያ ማዕከልን ጎብኝቷል።
እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ፣ ምክትል ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን በጋራ በመሆን የማዕከሉን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ፤ እስካሁን በ39 ሺህ 723 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ገለልተኛ ታዛቢዎች ተሰማርተው ሂደቱን ሙሉ በሙሉ እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በተጨማሪም 41 ሺህ 978 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በታዛቢነት መገኘታቸውና ሂደቱን በነጻነት እየታዘቡ መሆኑ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ከየምርጫ ጣቢያዎች የሚላኩለትን የድምጽ መስጫ ቀን የትዝብት ሪፖርቶች በይፋ መቀበል ጀምሯል።
ለጠቅላላ ምርጫው የአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ የየራሳቸውን ታዛቢ ቡድኖች በኢትዮጵያ በይፋ አሰማርተዋል።
በዚህም መሠረት 59 አባላት ያሉት የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እየተመራ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፤ ኢጋድ በበኩሉ 26 አባላት ያሉት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አሰማርቷል።
በምርጫው ከዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ታዛቢዎችም በሰፊው ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
በሀገር ውስጥ የተደራጁ 55 ሲቪክ ማኅበራት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን 1 ሺህ 562 የምርጫ ታዛቢዎችን በተለያዩ ጣቢያዎች ላይ አሰማርተዋል።
በሶስና አለማየሁ
#ኢትዮጵያ #ኢትዮጵያእየመረጠችነው #በምርጫብቻ #ፋናዲጂታል #Election #fanadigital #Ethiopia #Ethiopiavotes #Democracy #fanatelevision