የሀገር ውስጥ ዜና

ምርጫው በሠላማዊ መንገድ እየተካሄደ ነው – የሐረሪ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች

By Melaku Gedif

June 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምርጫው ድምፅ አሰጣጥ ሒደት ያለምንም ችግር እየተካሄደ ነው አሉ በሐረሪ ክልል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እየተወዳደሩ የሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች ተወዳዳሪዎች፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን ወክለው በክልሉ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እየተወዳደሩ የሚገኙት አስፋቸው ባልቻ÷ የድምፅ አሰጣጡ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎችም ለመራጮች ተገቢውን ገለፃ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ለክልሉ ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወ/ሮ ሐሰነት ሙሜ፣ ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ አብዱልሃፊ አሕመድ እና ከሐረር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሁሴን ሱሊይማን በበኩላቸው÷የምርጫው ድምፅ አሰጣጥ ከማለዳ ጀምሮ በሠላማዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

መራጩ ሕዝብም በነፃነት ድምፁን ለፈለገው ፓርቲ እየሰጠ መሆኑን የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎቹ አመልክተዋል፡፡

የምርጫ ካርድ የወሰዱ እና እስከ አሁን ወደ ምርጫ ጣቢያ ያልሄዱ መራጮች ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን ለመምረጥ የድምፅ መስጫው ከመጠናቀቁ በፊት ለፈቀዱት ፓርቲ ድምፃቸውን ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተሾመ ኃይሉ