አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብቱን በመጠቀም ድምጹን እየሰጠ ነው አሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ (ዶ/ር)፡፡
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የምርጫ ሒደቱ በተቀናጀ መንገድ እየተካሄደ ነው፡፡
ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ዜጎች ድምፅ እየሰጡ መሆኑን አንስተው÷ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ልጆቻቸውን የያዙ እናቶች፣ ወጣቶች እና አዛውንቶች ሳይቀሩ ከማለዳው ጀምሮ ድምጽ እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጭምር የምርጫ ሒደቱን ስኬታማ በሆነ መንገድ እያካሄደች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የምርጫ ታዛቢዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ያለውን እንቅስቃሴ እየቃኙ ነው ያሉት ስፔሲዮዛ ዋንዲራ (ዶ/ር) ÷ በሁሉም አካባቢ የድምፅ መስጠት ሒደቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የታየበት ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ