የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የጠላት ጩኸት ሳያስቆማቸው በነቂስ ወጥተው ድምጽ የሰጡ ዜጎችን አመሰገኑ

By Melaku Gedif

June 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂም ተአምረኛም ሕዝብ ነው ብለዋል።

ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅና ሊገመግም የሚችል ማን ነው፤ የዳበረ ባህል፣ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል ሲሉም አውስተዋል፡፡

በዛሬው ታሪካዊ ዕለት የሌሊቱ ብርድና ጨለማ ያላስፈራቸው፣ የቀትሩ ፀሐይና ድንገተኛ ዝናብ ያልበገራቸው፣ ሠርግ፣ ኀዘን፣ ወሊድና ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶች ያላገዳቸው እና ረጃጅም ሰልፎች ያላታከታቸው ዜጎች መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የአካል ጉዳት ድምጽ ለመስጠት ያልገደባቸው፣ ሕመምና እርጅና የሀገር ተስፋን ከማየት ያላገዳቸው፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ጨቅላ ልጃቸውን ማዘል ያላደከማቸው፣ ከምንም በላይ የጠላት ጩኸትና ማስፈራሪያ ያላስቆማቸው ዜጎችን አድንቀዋል፡፡

በብዙ ውጣ ውረዶች መካከል ያሳያችሁት ጽናት ለዴሞክራሲና ለሀገር ሕልውና የተከፈለ ነውና ከልብ የመነጨ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ይሄንን ሕዝብ ማገልገል መታደል ነውና ተመራጮች ያከበራችሁን አክብራችሁ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋጋ የከፈለውን ይሄንን ሕዝብ በንጽሕና ለማገልገል ያብቃችሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።