አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀጨኔ አካባቢ ለብዙኃን አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ ለምቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ በምርጫ ማግስት የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና የአገልግሎት መስጫዎች በጠቅላይ ሚኒስትራችን ተመርቀው ለሕዝብ ክፍት አድርገናል ብለዋል።
በከተማችን ለሚገኙ ለብዙዎቹ ወንዞች መነሻና የከተማችን ሳምባ የሆነው ደን የሚገኝበት ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ ያለው አካባቢ ወደ ተፈጥሯዊ ይዘቱ ተመልሶ የአካባቢውን ማህበረሰብ አኩሪ የስራ ባህል የሚዘክሩ ሐውልቶችና ቅርሶች ተገንብተውለት አካባቢው ፍፁም ማራኪ እና የሚያስደንቅ ገፅታን ተላብስሶ ተጠናቅቋልም ነው ያሉት።
የቀጨኔ አካባቢ ከዚህ ቀደም ለሰው ኑሮ ምቹ ያልሆነ፣ ለአደጋ የተጋለጠ እና የተጎሳቆለ መሆኑን አንስተው÷ ይህንን መልሶ በማልማት ውስን የሆነውን የከተማዋን የመሬት ሀብት ለብዙኃን አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ ለምቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አመልክተዋል።
597 ሄክታር ቦታ እና 9 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለመዝናኛ፣ ለንግድና ለተለያዩ ማሕበራዊ ኩነቶች ተስማሚ በሆነ መልኩ የተገነባ ሰፊ የከተማ መናፈሻ እንደሆነም ገልጸዋል።
በከተማ ግብርና ስራዎች 15 ሄክታር ቦታ በአረንጓዴ የተሸፈነ ሲሆን÷ ቀሪው ደግሞ በ210 ቀፎ ዘመናዊ ንብ እርባታ፣ በአበባ ጋርደን እና በእጽዋት ጋርደን ለምቷል ብለዋል።
እንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ያካተታቸው ሌሎች መሰረተ ልማቶች፦
👉6.4 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መንገድ፣ 8 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 22 ክሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 4 ኪሎ ሜትር ሃይኪንግ መንገድ፣ 39 ቼክ ዳም ተገንብተዋል።
👉2 አዲስ የተሽከርካሪ ድልድዮች ሲገነቡ፣ 3 ነባር የተሽከርካሪ ድልድዮች እድሳት ተደርጎላቸዋል። እንዲሁም ሌሎች የእረንጓዴ ልማት ጥንቅቅ ብለው ለምተዋል።
የከተማችን ነዋሪዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ከንቲባዋ÷ ይህንን ልዩ ሆኖ የተጠናቀቀ የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት አዕምሮችሁን ዘና አካላችሁን ፈታ እያደረጋችሁ እንድትገለገሉበት እና ረጅም አገልግሎት እንዲሰጥ እንድትንከባከቡት አደራ እላለሁ ብለዋል።