አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የታቀደውን የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት አመራሩ የሚባክን ጊዜ ሊኖረው አይገባም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የመልሶ ማልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፎ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በመምረጥ ታሪካዊ ጥንካሬ አሳይቷል።
ዛሬ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በቀጥታ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ የታቀደውን የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በእንጦጦ ተራራ ላይ የተሞከረው የኢንጆሪ ልማት ከፍተኛ ውጤት ማሳየቱንና ከዚህ በተጨማሪም ብርቱካን፣ ሎሚ፣ የደጋ ቡና እና ልዩ ማር እየተመረተ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲሁም የባሕር ዛፍን በማስወገድ በምትካቸው ሀገር በቀል ዛፎችን የመትከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም የተራራውን ውሃ የመያዝ አቅም ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በተራራማው አካባቢ አፈር እንዳይሸረሸር በኮንሶ ሙያተኞች የተገነቡት እርከኖች የሚደነቁ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም የገጠር እውቀትን ለከተማ ልማት የመጠቀም ትልቅ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በወንዙ ዳርቻ የነበሩት የተጨናነቁ ቤቶች ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡና ለመንገድ የማይመቹ እንደነበሩ አስታውሰው÷ አሁን ግን አካባቢው ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ለሰዎች መዝናኛና እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከእንጦጦ እስከ ቦሌ ያለው የሸገር ፕሮጀክት በአብዛኛው መጠናቀቁንና የቀሩት ክፍሎች በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ጠዋት ጠዋት በዚህ የልማት መስመር ላይ በእግር በመጓዝ ጤናቸውን እንዲጠብቁና የሀገራቸውን ውበት እንዲያደንቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ሥራው በሀገር በቀል ወጣቶችና አርቲስቶች የተሰራ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሀገሪቱ የምትፈልገውን እድገት ለማምጣት ብቸኛው አማራጭ ተግቶ መስራት መሆኑን አሳስበዋል።
በዮናስ ጌትነት