የሀገር ውስጥ ዜና

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት ሆኖ አልፏል – ኮሚሽኑ

By Yonas Getnet

June 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት ሆኖ ማለፉን አረጋገጠ።

ኮሚሽኑ የመጀመሪያ ደረጃ የግኝት ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሰፊ የክትትል ሥራ ማከናወኑን ገልጿል።

በዚሁም የድምፅ መስጫ ቀኑ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያልተፈጸመበት ሆኖ ማለፉን አረጋግጧል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ ምርጫው የተለመዱ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ፣ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ተከናውኗል።

ኮሚሽኑ የምርጫውን ሂደት በላቀ ደረጃ ለመከታተል ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን በማንሳት በዕለቱም 104 የክትትል ቡድኖችን በማዋቀር እና ከ320 በላይ አባላትን በመመደብ ከ3 ሺህ በላይ በሆኑ የምርጫ ጣቢያዎችና ከ180 በላይ የምርጫ ክልሎች ላይ የክትትል ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

የክትትል ቡድኑ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በአካል በመገኘት ጭምር የምርጫውን ውሎ በንቃት መከታተሉን አስረድተዋል።

ከመስክ ምልከታው በተጨማሪ በዋና ኮሚሽነሩ፣ በምክትል ኮሚሽነሮችና በ4 የዘርፍ ኮሚሽነሮች የተዋቀረ ልዩ የክትትል ቡድን በዋናው መሥሪያ ቤት የልዩ ሁኔታዎች መከታተያ ክፍል በማቋቋም ሂደቱን በቅርበት ክትትል ማድረጉን ጠቁመዋል።

በሂደቱ በአጠቃላይ 104 አቤቱታዎች መቅረባቸውን ገልጸው÷ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ተጨማሪ መረጃ የሚፈልጉ እንዲሁም አራቱ በአሁኑ ሰዓት በሂደት ላይ ያሉ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ በሙሉ ተገቢውን ፈጣን መፍትሔ ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

በፍቅርተ ከበደ