አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምርጫው ሂደት የታዩ አዎንታዊ ጅምሮችን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል አለ የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።
የጋራ ምክር ቤቱ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጠው መግለጫ÷ በምርጫው ሂደት የታዩ አዎንታዊ ጅምሮችን ይበልጥ በማጠናከር የሂደቱን ሰላማዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ ነፃነትና በሕዝብ ዘንድ ያለውን ታማኝነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን ውሳኔና ድምፅ በአክብሮት ሊቀበሉ እንደሚገባ በመግለጽ÷ ፓርቲዎችም ደጋፊዎቻቸውን ወደ ሰላም፣ መከባበርና ሕጋዊ አሠራር በመምራት እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት ልዩነቶች በውይይትና በሕግ ማዕቀፍ ብቻ እንዲፈቱ አስገንዝቧል።
የምርጫው ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ መሠረት ተረጋግጦ በይፋ እስከሚገለጽ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሂደቱን በትዕግሥትና በኃላፊነት ስሜት እንዲጠባበቁ ጠይቋል።
ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክርና የመግባባት ባሕል እንዲጠናከር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ መግለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
በመጨረሻም የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይትና በዴሞክራሲያዊ ሂደት የመፍታት ባሕልን ማጠናከር እንደሚገባ የገለጸው የጋራ ምክር ቤቱ÷ የትብብርና የፉክክር ሚዛንን በአግባቡ በማስጠበቅ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓትን በሀገሪቱ ማጠናከር እንደሚገባ አብራርቷል።