አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር መሰረት የሚጥል ነው አለ፡፡
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሱዌሳ ዋንዳራ ካዙቤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢጋድ ያደረገውን የታዛቢነት ሚና አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው እንዳሉት÷ ኢጋድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀረበለት ግብዣ መሰረት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታዛቢነት ሚናውን ሲወጣ ቆይቷል።
ኢጋድ 11 የታዛቢ አባላትን በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በማሰማራት ምርጫውን መከታተሉን ጠቁመው÷ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ምክክር ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ኢጋድ በነበረው ትዝብት ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች፣ ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች እና ከ42 በላይ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ ችግር ካለባቸው የትግራይ ክልል እና ከአማራ ክልል ጥቂት አካባቢዎች ውጭ በሌሎች አካባቢዎች ምርጫ መደረጉንም አንስተዋል።
የመራጮች ትምህርት ለመስጠት 169 የሲቪል ማህበራት መሰማራታቸውን ጠቅሰው÷ መገናኛ ብዙኃን ለፓርቲዎች የሰጡትን የአየር ሰዓት ድልድል እና አሳታፊነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ሥራዎችን ኢጋድ እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያለው እና አካታችነትን ያረጋገጠ እንደነበርም አስረድተዋል።
በሚኪያስ አየለ