የሀገር ውስጥ ዜና

በምርጫው አካታችነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው – ኢጋድ

By Hailemaryam Tegegn

June 03, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው አለ፡፡

ምርጫውን የታዘቡት ኢጋድና አፍሪካ ኅብረት የመጀመሪያ ዙር ሪፖርታቸውን በተመለከተ መግለጫ እየሰጡ ነው፡፡

የኢጋድ ታዛቢዎች ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ እንዳሉት÷ ኢጋድ በሂደቱ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድምፅ አሰጣጥ የነበሩ ሒደቶችን ገምግሟል።

በሒደቱ አዳዲስ አሰራሮችና ዓለም አቀፋዊ የምርጫ አሰራር መርሆዎች መተግበራቸውንና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አንስተዋል።

ለመራጮች ትምህርት ለመስጠት 169 የሲቪል ማህበራት መሰማራታቸውን ገልጸው፥ መገናኛ ብዙሃን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት መደልደላቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡

አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ተሳትፎ በማረጋገጥ ምርጫው አካታች እንዲሆን የተሰሩ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢጋድ በድምፅ መስጫው ቀን በ7 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች በአጠቃላይ 11 የታዛቢ ቡድን ያሰማራ ሲሆን፥ የድምፅ አሰጣጡ ህጋዊ መሆኑንና ቁሳቁሶቹ በአግባቡ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

በምርጫ ጣቢያዎቹ ረጃጅም ሰልፎች መታየታቸውን የገለጹት ቡድን መሪዋ፥ ሕዝቡ በትዕግስትና በጨዋነት ላሳየው ተሳትፎ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለሰላምና ለዲሞክራሲ ግንባታ ላሳያችሁት ስኬታማነት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በአፈወርቅ እያዩ