አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቶውት ሊደር አፍሪካ ከተሰኘ የኖርዌይ ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ጋር በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም ላይ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና ዘመናዊ የኃይል አጠቃቀምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ለልምድ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረጅም ዓመታት የበለጸገ ልምድ ያላትን የኖርዌይን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደሚያስችልም ተጠቅሷል፡፡
ይህም ለአምራችና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቅም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተገለጸው፡፡
ስምምነቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋትና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማስፈን ለተጀመረው ስትራቴጂካዊ ጉዞ ትልቅ አጋዥ እንደሚሆን መገለጹን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጌቱ ገረመው (ኢ/ር)፣ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቴይን ክሪስቴንሰን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።