አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማከናወኗ ኢትዮጵያውያን ልትኮሩ ይገባል አሉ የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንን የመሩት ኡሁሩ ኬንያታ ከኢጋድ የታዛቢ ቡድን ጋር በመሆን የምርጫውን የመጀመሪያ ሪፖርት በትናንትናው ዕለት አቅርበዋል፡፡
በዚህ ዕለት ኢትዮጵያውያን ምርጫው በስኬት በመጠናቀቁ ሊኮሩ እንደሚገባ በአጽንኦት መናገር እፈልጋለሁ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደማቅ ታሪኩን ሊዘክር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ በንግግራቸው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሆን የቅኝ ግዛት ማዕበልን ተቋቁመው ፍጹም በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ማጽናታቸውን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና ራስን የማስተዳደር መብት ተጋድሎ ማድረጓን አስታውሰው፥ ይህም የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት፡፡