የሀገር ውስጥ ዜና

የአቡዳቢ የልማት ፈንድ በኢትዮጵያና አፍሪካ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እየተከታተለ ነው

By Melaku Gedif

June 03, 2026

የአቡዳቢ የልማት ፈንድ በአፍሪካ በተለያዩ ዘርፎች የሚያከናውናቸውን ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአቡዳቢ የልማት ፈንድ በአፍሪካ ሀገራት የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማሳለጥና የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታን ለማጠናከር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህ ሰመረትም በኢትዮጵያ፣ በቶጎ፣ በማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ እና በሌሎች ሀገራት እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማት ሥራዎችን አፈጻጸም በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አሁን ላይም በ37 ሚሊየን ድርሃም ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የቶጎ መንገድ ልማት 92 በመቶ የደረሰ ሲሆን÷ በ110 ሚሊየን ድርሃም የሚገነባው የማዳጋስካር መንገድ ልማት ደግሞ 80 በመቶ ተጠናቅቋል፡፡

እንዲሁም በ165 ሚሊየን ድርሃም ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የናይጄሪያ መንገድ ፕሮጀክት 45 በመቶ አፈጻጸም ላይ መድረሱ ነው የተመላከተው፡፡

እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ሥራ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ተጠናቅቆ የሀገራቱን ዜጎች ሕይወት ለማሻሻል እንዲያስችል በቁርጠኝነት የክትትል ሥራ እንደሚሰራም ተጠቅሷል፡፡

የተጠቃሚ ሀገራትን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማሳካት ይሰራል ያለው የልማት ፈንዱ÷ ለዚህም አቅምን በተገቢ ሁኔታ መጠቀምና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር መተግበር እንደሚገባ ጠቅሷል፡፡

የአቡዳቢ የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት እድገትን ለማሳለጥና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ውጤታማናት ለማጠናከር ከፍተኛ መሰረት እየጣለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የልማት ፈንዱ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ከ10 ሚሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን÷ በዚህም የጌዴኦ- ፊንጫ-ለምለም በረሃ መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መከናወኑ ተመልክቷል፡፡

80 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገዱ የጌዴኦ ካባቢዎችን ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር በማስተሳሰር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

በሌላ በኩል የልማትፈንዱ በኢትዮጵያና አፍሪካ በታዳሽ ኃይል፣ በትምህርት፣ ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ መሰረተ ልማት፣ በሰብዓዊ እርዳታ እና ሌሎች ዘርፎች የሚገጥሙ ተግዳሮችን በመቅረፍ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡

የአቡዳቢ የልማት ፈንድ ኢኒሼቲቭ በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማጠናከር በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን እና ማህበራዊ ልማትን ለማሳለጥ ያለመ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተገለጸው፡፡