ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢጋድ በሶማሊያ የተፈጠረው ቀውስ በአካታችና ሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ

By Melaku Gedif

June 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በሶማሊያ የተፈጠረው አለመረጋጋት በአካታችና ሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ምላሽ መስጠታቸው ተመላክቷል፡፡

ኢጋድ ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ÷ ሁሉንም የጥቃት ድርጊቶች በጽኑ ኮንኗል፡፡

በሶማሊያ የፖለቲካ ውጥረቱ ከፍ ባለበት ወቅት በሞቃዲሾ የተፈጠረው አለመረጋጋት አሳሳቢ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ሁሉም ወገኖች ውጥረቱን እንዲያረግቡና እና ልዩነቶቻቸውንም በሰላማዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ገንቢ በሆነ ውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ሰላምን እና መረጋጋትን ማጽናት እንዲሁም ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ለሶማሊያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ጥረት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝቧል፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሶማሊያን ሕዝብ ጥቅም በማስቀደም ሰላማዊ መፍትሔዎችን የማፈላለግ መንገድ እንዲከተሉም ኢጋድ አሳስቧል።

ሶማሊያ የኢጋድ መስራች አባል ሀገር እንደመሆኗ ለቀጣናው ሰላም፣ ደህንነት እና ልማት ማዕከል ሆና መቆየቷን መግለጫው አውስቷል።

ኢጋድ ከሶማሊያ ጋር በመተባበር ብሔራዊ አንድነት እና ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።