ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማሙ

By Hailemaryam Tegegn

June 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ሄዝቦላህን ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎችን በማስወጣት የሊባኖስ ጦር ብቻ የሚቆጣጠራቸው አካባቢዎችን ለመመስረት መስማማታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ሀገራቱ ስምምነት ላይ ቢደርሱም ሄዝቦላህ በዛሬው ዕለት በእስራኤል ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፥ በተመሳሳይ የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት ፈጽሟል ሲል ወንጅሏል፡፡

ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ አለመኖሩ ከእነዚህ ድርድሮች የሚመጡ የማዕቀፎች ትግበራ ውጤታማነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

እስራኤል እና ሊባኖስ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለተጨማሪ ንግግሮች እንደሚገናኙ ተገልጿል።

ሄዝቦላ በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ኢራንን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን፥ ይህም እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት እንዲባባስ ማድረጉን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡