የሀገር ውስጥ ዜና

ምርጫውን ለማደናቀፍ የታሰበውን ሴራ በማምከን የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ የጸጥታ ሥራ ተሰርቷል

By Hailemaryam Tegegn

June 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ጠላቶች የተቀናጀውን ከፍተኛ ሴራ በማምከን የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል አለ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ በምርጫው የፀጥታና ደኅንነት አፈፃፀምን በመገምገም በቀጣይ ሒደቶች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የጋራ ግብረ ኃይሉ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያሉ ስራዎችን እንደ ሀገር ዕቅድ አውጥቶ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም በተግባር የተፈተሸ፣ የተናበበና ሰላምን ለማፅናት ጀግንነት የታየበት ተግባር በመፈፀሙ ምርጫው በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል ብለዋል።

ምርጫው በሰላማዊ መንገድ መካሄዱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ በተሰራው ሪፎርም አሁን ላይ በተጨባጭ ትላልቅ ተልዕኮዎችን በብቃት መወጣት የሚችሉ ፀጥታ ተቋማት መፈጠራቸውን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

ምርጫውን ለማደናቀፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ጠላቶች የተቀናጀውን ከፍተኛ ሴራ ያከሸፈና የሀገርን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ እንዲሁም የሪፎርሙ ውጤት በተግባር የታየበት የጸጥታና ደህንነት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ ሁሉንም በሚዛን አስቀምጦ የምርጫው ቀን ሲደርስ የሀገር አንድነትና ሉአላዊነትን ያጸና ተሳትፎ አድርጓል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ መንግስት በካርድ እንጂ በጥይት አይሆንም የሚል መልዕክት ያስተላለፈበት ምርጫ መሆኑን ገልፀዋል።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በቀጣይም በሽብርተኞችና በፅንፈኞች ላይ የተጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡

በቀጣይም ሕዝባዊና መንግስታዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፀጥታ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡