የሀገር ውስጥ ዜና

የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ ተካሂዷል – የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር

By Yonas Getnet

June 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ ተካሂዷል አለ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር።

ማሕበሩ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና ደኅንነት ለመገምገም ያከናወነውን የምልከታ ሥራ መሠረት ያደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በበጎ ፈቃደኝነት የተሰማሩ 60 ታዛቢዎችን በዘጠኝ ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ 136 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ማሰማራቱን ገልጿል።

በምርጫው ላይ የታዛቢ ቡድኑ ምልከታ ባደረገባቸው ጣቢያዎች በአብዛኛዎቹ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ የምርጫው ሂደት መጠናቀቁን አመልክቷል።

በምርጫ ጣቢያዎች የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ሁሉንም ያካተተና ስልታዊ የሆኑ መዋቅራዊ ጥሰቶች ያልታዩበት መሆኑንም ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

በሂደቱ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በግልጽ የታየ በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች፣ የሚያጠቡ ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ድምፅ እንዲሰጡ የተደረጉበት አዎንታዊ አሠራር ተስተውሏል ነው ያለው።

ማሕበሩ አሁን ያወጣው ሪፖርት የመጀመሪያ ደረጃ መግለጫ መሆኑን በመጠቆም ከምርጫ በኋላ ያለውን ሁኔታ መከታተሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሙሉ የመረጃ ትንተናን ያካተተ የመጨረሻ ሪፖርቱን ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን ለመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ለመጠቀም ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ እንደሆነም አመልክቷል።