የሀገር ውስጥ ዜና

ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው – ምሁራን

By Yonas Getnet

June 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ባህል መዳበር በከፍተኛ ደረጃ የታየበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር አርአያ የሚሆን ነው አሉ ምሁራን።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ወንደሰን ጀረኒ (ዶ/ር) ÷ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ የሐሳብ ሙግትን በማቅረብ የተሻለ አማራጭ በካርድ እንዲወሰን የሚፈቀድበት ሒደት ነው ብለዋል፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሒደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው ታማኝነትና ቁርጠኛነት የተሞላበት ሒደት ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ከምዝገባ ሒደቱ ጀምሮ የነበሩት አሠራሮች ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ ጥርጣሬዎችን ያጠፉ፣ የተረጋጉ እና ታማኝነት የተሞላባቸው እንደነበሩ ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲን በተግባር ማሳየት የሚከብድ ነገር እንዳልሆነ እና በባሕልም ሆነ በተለያዩ ታሪካዊ ሥርዓቶች ሲለማመዱ የመጡትን እሴት ዛሬ በካርድ እና በድምጻቸው አረጋግጠዋል ነው ያሉት፡፡

በድህረ ምርጫ ወቅት ውጤቱ በይፋ እስኪገለጽ ድረስ ሕጋዊ ሒደቱን በትዕግሥት መከተል እንደሚገባ ጠቁመው÷ ፓርቲዎች የሕዝብን ድምጽ በአክብሮት ለመቀበል መዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሶሺዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር የሆኑት ኢዮብ ደፈርሻ በበኩላቸው÷ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉ በነቂስ ወጥቶ የሚፈልገውን እንደመረጠ አስታውሰዋል፡፡

ይህም አዲሱ ትውልድ በካርድ እና በዴሞክራሲያዊ አሠራር ላይ ያለውን ጽኑ እምነት የሚያሳይ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ሕዝቡ ፀሐይም ሆነ ብርዱድ ሳይበግረው፤ የታመሙ ዜጎች ጭምር ከአልጋቸው ተነስተው ድምፅ ሲሰጡ መመልከታቸውንና ይህም ሕዝቡ የተሰጠውን መብት በተሟላ ብስለት የተገበረበት መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።

የምርጫ ሒደቱ ፍጹም ሰላማዊ እንደነበር ገልጸው÷ በቀጣይ አጠቃላይ ውጤቱ ሲገለጽ ተፎካካሪዎች የሕዝብን ውሳኔ በጸጋ የመቀበል ፖለቲካዊ ጨዋነት ሊያሳዩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ምሁራኑ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ምርጫው እንዳይካሄድ እና ስኬታማ እንዳይሆን ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ እና ውዥንብር ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን መሰል መሰረተ ቢስ ሃሳቦችን ወደ ጎን በመተው በነቂስ ወጥቶ ዴሞክራሲ ብቸኛ ምርጫው መሆኑን አሳይቷል ብለዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት