የሀገር ውስጥ ዜና

አካባቢን በኹነት ወይስ በተግባር እንጠብቅ …

By Abiy Getahun

June 05, 2026

የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ለኢትዮጵያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ የዘለለ የተግባር እና የሕልውና ትርጉም አለው፡፡

ቀኑ በየዓመቱ ጁን 5 (በኢትዮጵያ ግንቦት 28) ይከበራል። በእርግጥ በዕለቱ በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) አስተባባሪነት ምድርን ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ለመታደግ እና የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን ለመመለስ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ይደረግበታል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ሃይል ማስፋፊያ፣ በኤሌክትሪክ ተንቀሳቃሽነት የአየር ንብረትን ለመጠበቅ በስፋት እየሰራች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ብክለት ምንም ድርሻ ሳይኖራቸው ተጎጂነቱን ግን ካደጉት ሀገራት እኩል ሲጋሩ ኖረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በድንበር አይገደብም፡፡ በአንድ አካባቢ የሚፈጠረውን ቀውስ ሁሉም ይጋተዋልና፡፡

ለዚያም ነው የጋራ ወደፊትን ለመጠበቅ ትብብር አስፈላጊ ነው በሚል ኢትዮጵያ በየአመቱ ከራሷም አልፋ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን እንዲጋሩ እያደረገች ያለችው፡፡

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት ይነገራል፡፡ በወቅቱ በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም የደን ሽፋናችን ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መደህየት እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውሃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ማህበረሰባችንን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) የሀሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተጀመረ፡፡

ከዚያን አመት ጀምሮ እንደ ሀገራዊ ንቅናቄ በመያዝ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም የሃገራችን አካባቢዎች የመትከልና የመንከባከብ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

በ2012 ዓ.ም 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን፣ በ2014 ዓ፣ም 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ 2016 ዓ.ም 7 ነጥብ 5 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 8 ቢሊዮን ችግኝ የተተከለ ሲሆን በ2018 ዓ.ም ዘንድሮ ደግሞ 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአንደኛው እና በሁለተኛው ምዕራፍ የተተከሉ ችግኞችን 50 ቢሊዮን ለማድርስ ግብ የታጣለ ሲሆን፣ ይህም ተግባር ሀገራችን በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሃ-ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

የፕሮግራሙ ውጤታማነት እና ስኬት የተገኘው ስራውን ሀገር አቀፍ በማድረግ፣ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ በማሳተፍ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ካለው ሀገራዊ የልማት ፋይዳ ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት፣ አድናቆት እና ምስጋና ያገኘ ሲሆን ሌሎች ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ለሚያደርጉት ጥረት ፕሮግራሙን በሞዴልነት መከተል ጀምረዋል፡፡

ለዚህም ነው የአካባቢ ጥበቃ የተግባር እና የሕልውና ጉዳይም ነው የምንለው፡፡