አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገሪቱ የሚገኙ የእምነት ተቋማት የማንኛውም የፖለቲካ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ሊሆኑ አይገባም አሉ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፡፡
ሚኒስትሩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፥ ሰሞኑን በአርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ሽብርተኛው ሸኔ በንጹሃን ላይ የፈጸማቸውን ጥቃቶች አውግዘዋል፡፡
በዞኑ አሰኮ ወረዳ ደለታ ጨፌ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት አራት ንጹሃን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን፥ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንዲሁም 65 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ በሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በሽብር ቡድኑ ታግተው የነበሩ በድምሩ አራት ንጹሃን መገደላቸውን ገልጸው፥ በዞኑ በተፈጸመው ጥቃት ስምንት የጸጥታ አካላት መሰዋታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ለማዛባትና የተለየ ቅርጽ ለማስያዝ የተደረጉት ሙከራዎች የሚወገዙ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደዚህ አይነት ክስተት ሲፈጠር ኅብረተሰቡን ወደ ግጭት ለማስገባት የሚደረጉ ሙከራዎች ተገቢ አለመሆናቸውን ገልጸው፥ የእምነት ተቋማት የማንኛውም የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሊሆኑ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከ6ሺህ በላይ አድባራትና ከፍተኛ ኃይማኖታዊ ቦታ የሚሰጣቸው በርካታ ገዳማት እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ እነዚህን የእምነት ስፍራዎች ለዘመናት ሲጠብቁ መቆየታቸውንም አውስተዋል፡፡