አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነድፈው የተተገበሩ ፕሮጀክቶች ለአካባቢ ጥበቃ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው አለ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፡፡
የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ53ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።
ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተመርቆ ክፍት የተደረገውን ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ የተሰራ የወንዝ ዳርቻ ልማት ጎብኝተዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነድፈው የተተገበሩ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት መርሐ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው÷ ይህም የአየር ብክለት መቀነስን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ ነው ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ ማስቻሉን ጠቁመው÷ ሥነ ምህዳርን በማሻሻል ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አካባቢ ጥበቃን ውጤታማ እያደረጉ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ እንደሆነና የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለዚህ አይነተኛ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
በፕሮጀክቱ ሀገር በቀል ዛፎች መተከላቸውን ገልጸው÷ ሀገር በቀል የኮንሶ የአካባቢ ጥበቃ እውቀቶች ዐሻራ ያረፈበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡
መሰል የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን ተምሳሌታዊና ተጠቃሽ ሀገር እያደረጋት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡