አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚሊሻ ኃይሉ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በልማትና የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ተግባር ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈ ነው አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የምስረታ በዓል አከባበርና የእውቅና መርሐ ግብር “የ30 ዓመታት የጀግንነት ታሪክ፤ ለዘላቂ ሰላም፣ ለሀገር ኩራት” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ የሚሊሻ ኃይሉ ላለፉት 30 ዓመታት የሕዝብና መንግሥት አደራን በመወጣት አኩሪ ታሪክ ሰርቷል።
ተግባሩን በማስቀጠልም የጠላቶችን ሴራ ለማክሸፍ ከፌዴራልና ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀትም ሰላምን በማስፈንና በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ግንባር ቀደም ተግባር ማከናወኑን ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የሚሊሻ ኃይሉ የ30 ዓመታት ጉዞ በዓል ሲከበርም ለሀገር፣ ለክልሉና ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመዘከር መሆኑን አስገንዝበዋል።