የሀገር ውስጥ ዜና

ቅሬታዎች በሕግና አሰራሩ መሰረት እየተመረመሩ ምላሽ እየተሰጠባቸው ነው – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

By Adimasu Aragawu

June 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ያጋጠሙ ቅሬታዎች በተቋሙ ሕግና አሰራር መሰረት እየተመረመሩ ምላሽ እየተሰጠባቸው ነው አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ እስካሁን ድረስ 31 ቅሬታዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም 16 ከግል እጩዎች በአጠቃላይ 47 ቅሬታዎች ቀርበዋል።

ቦርዱ ቅሬታዎችን ተቀብሎ የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ምርመራው እንደተጠናቀቀ የመጨረሻ ውሳኔውን ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የቀረቡ ቅሬታዎችን በሕጋዊ መንገድና በገለልተኝነት ለመዳኘት የሕግ ባለሙያዎች ጉባኤ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።

በምርጫ ሂደት ያጋጠሙ ጥቆማዎችንና ቅሬታዎችን በኦፕሬሽን ዴስክ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዛቢዎች ዴስክ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በተመሰረተ የጋራ የዋትስአፕ መድረክ እንዲሁም በ7555 እና 6412 አጭር የጥሪ መስመሮች አማካኝነት ሲያሰባስብ መቆየቱን አመልክተዋል።

በዚህም ቦርዱ ቅሬታዎቹ እንደደረሱ ፈጣን ርምጃዎችን እንደወሰደ አስረድተዋል።

በምርጫው ሂደት ጣልቃ የገቡ የአስተዳደር አካላት ከጣቢያዎች እንዲርቁ እንደተደረገ እና የጥሰት ተግባር በፈጸሙ አስፈጻሚዎች ላይ ከሥራ ማሰናበት እንዲሁም ጣቢያዎችን እስከመዝጋት የደረሰ ርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።

በብርሃኑ አበራ