አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በበጀት ዓመቱ 158 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ምርት ማምረት ጀምረዋል አለ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የቢሮ ምክትል ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መጥቷል።
በተለይም ባለሃብቱ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንዳስቻለ ገልጸው ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት ባሻገር የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እያገዘ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ወራት ብቻ በኢትዮጵያ ታምረት ንቅናቄው 158 መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ማምረት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
“ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ኃሳብ እየተካሄደ ባለው በዚህ መርሐ ግብር ላይ 145 ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እያስተዋወቁ እንደሚገኙ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡