የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ስኬት ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አደም ፋራህ

By Mikias Ayele

June 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውነተኛ ዴሞክራሲን ከልማትና ከሰላም ጋር በማጣመር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ስኬት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ።

ላለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል ሸቤሌ ሪዞርት ከብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲካሄድ የቆየው የምክክርና የግምገማ መድረክ ተጠናቅቋል።

አቶ አደም ፋራህ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በመድረኩ ላይ እስከ ምርጫው ዕለት የነበረው የብልጽግና ፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም እና በድህረ ምርጫ ሥራዎች ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።

ለዚህ ታሪካዊ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱት የምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ ታዛቢ ተቋማት እና በፅኑ ቁርጠኝነት ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፈው ሕዝብ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከመድረኩ ጎን ለጎን አመራሩ በጅግጅጋ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን መጎብኘቱን እና በክልሉ መንግሥትና በሕዝቡ ጥረት እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን መመልከቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየረውን የኮሪደር ልማት ሥራ፣ ለጸጥታ ኃይሎች የላቀ የጤና አገልግሎት የሚሰጠውን አዲሱን የፖሊስ ሆስፒታል እንዲሁም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋምን መጎብኘታቸውን አብራርተዋል።

በጅግጅጋ የታዩት ፈጣን ለውጦች የብልጽግና ፓርቲን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፖሊሲዎች ውጤታማነት በተግባር ያረጋገጡ እና ለሌሎች አካባቢዎችም አርአያ የሚሆኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት እውነተኛ ዴሞክራሲን ከተጨባጭ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ስኬቶች ጋር በማጣመር፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በተግባር የማረጋገጥ ስኬት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።