የሀገር ውስጥ ዜና

ለትውልድ የሚሻገሩ መሰረተ ልማቶች …

By Mikias Ayele

June 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገረ መንግሥት ግንባታ በመሠረተ ልማት፣ በተቋማት፣ በሰው ኃይል ልማት እና በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ላይ የሚደረግ የተቀናጀ ሥራ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግራ ዛሬ ወደ እድገትና ዘላቂ ልማት የሚያመራ ጉዞ ላይ ትገኛለች።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ የተሻለ ኑሮ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የተረጋጋ ሀገር ለማስረከብ ያለመ ነው።

መንገዶች፣ ድልድዮች፣ አየር ማረፊያዎች እና እንደ ከተማ ልማት ፕሮጀክቶች ያሉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የአንድን ሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያፋጥኑ መሠረታዊ ግብዓቶች ናቸው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከናወኑ የመንገድና የከተማ ልማት ሥራዎች የንግድ እንቅስቃሴን እያሳደጉ ሲሆን፤ የሕዝብን ተደራሽነትና የኑሮ ጥራት ለማሻሻል እያገለገሉ ይገኛሉ።

ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በረጅም ጊዜ የሀገሪቱን የምርት እና የንግድ አቅም በማጠናከር ለትውልድ የሚተላለፉ ሀብት ናቸው።

የሀገር እድገት ከኃይል አቅርቦት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ በስፋት ተሰርቷል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮችን ማስፋፋት ኢንዱስትሪዎችን ለማጎልበት፣ የገጠር ልማትን ለማፋጠን እና የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ትልቅ ሚና አለው።

በዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የውሃ፣ የፀሐይ እና የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች በቀጣይነት በመገንባት ላይ ይገኛሉ ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ለዛሬው ትውልድ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለመጪው ትውልድ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት መሰረት ይሆናሉ።

የምግብ ዋስትና እና የኢንዱስትሪ እድገትም የሀገረ መንግስት ግንባታ ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው።

የመስኖ ልማት፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የሀገሪቱን የምርት አቅም ያሳድጋሉ።

የሀገር ውስጥ ምርት ሲጨምር ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ይቀንሳል፤ የወጣቶች ሥራ እድልም ይሰፋል፤ ይህም ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ይሆናል።

ሌላው የሀገር እድገት መሠረቱ የሰው ኃይል ሲሆን፤ የትምህርት እና የጤና ተቋማት የሰለጠና ጤናማ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ሚናቸውን እየተወጡ ነው።

የትምህርትና የጤና ኢንቨስትመንቶች በቀጣይ ትውልድ ላይ የሚያሳድሩት ገንቢ ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ሀገረ መንግስት ግንባታ በአንድ ቀን የሚጠናቀቅ ሥራ ሳይሆን በራዕይ፣ በትጋት እና በትውልድ ተሻጋሪ አስተሳሰብ የሚገነባ ሂደት ነው።

በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት እና የጤና ፕሮጀክቶች ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ ዘላቂ መሠረት እየፈጠሩ ነው።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ስኬት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ከማፋጠን ባለፈ መጪውን ትውልድ የሚያኮራ ጠንካራ ሀገር ለማስረከብ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

በአመለወርቅ ደምሰው