ስፓርት

የኢራን የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድን ሜክሲኮ ገባ

By Mikias Ayele

June 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጥምር በሚያስተናግዱት የ2026 ዓለም ዋንጫ የሚሳተፈው የኢራን ብሔራዊ ቡድን ሜክሲኮ ገብቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ሜክሲኮ ያቀናው ከአሜሪካ ቪዛ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ውስጥ በመግባቱ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ በሜክሲኮዋ ቲጁዋና ከተማ ዛሬ ከሰዓት የደረሰ ሲሆን፤ ልምምዱን በቲጁዋና በማድረግ ለምድብ ጨዋታዎች ብቻ ወደ አሜሪካ ስታዲየሞች ያቀናል።

ቀደም ሲል የኢራን ብሔራዊ ቡድን 15 አመራሮች እና ድጋፍ ሰጭ አባላት የአሜሪካ ቪዛ መከልከላቸውን በመግለፅ፤ ጉዳዩ በስፖርት ላይ የተደረገ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነው ሲል አውግዟል፡፡

የኢራን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ፣ ምክትላቸው እና የሚዲያ ዳይሬክተሩ የአሜሪካ ቪዛ ከተከለከሉት የኢራን ብሔራዊ ቡድን አባላት መካከል እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው÷ ኢራን ከኒውዚላንድ ጋር ጨዋታዋን ከምታደርግበት 10 ቀን አስቀድሞ ለሁሉም የኢራን ተጫዋቾች እና የድጋፍ ሰጪ የቡድን አባላት ቪዛ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ኢራን አግባብነት የሌለው ክስ በማቅረብ አሸባሪዎችን ወደ አሜሪካ ለማስገባት እየሞከረች ነው ያሉት ባለሰልጣናቱ÷ በተለይም ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም የስፖርት ልዑካን ወደ ዋሽንግተን እንደማይገቡ ገልጸዋል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ በኢራን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከተካተቱ ተጫዋቾች አብዛኛው ብሔራዊ ውትድርናን ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

የዓለም ዋንጫው በፈረንጆቹ ሰኔ 11 የሚጀመር ሲሆን የዓለም ዋንጫው ሲጀመር አሜሪካ በታሪክ ጦርነት የገጠመቻትን ሀገር በእግር ኳስ ያስተናገደች ብቸኛ ሀገር እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

በሚኪያስ አየለ