ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ክስተቶችን እንተንብይ፡፡ እድሎችን እና ፈተናዎችን እንደ ሀገር ቀድመን እንረዳ፤ ሀገር ለማዳንና ለመገንባት ዛሬ እንዘጋጅ፡፡
ይህ እሳቤ እንደ ማህበረሰብ ካለፈው ተምረን፣ የዛሬን ተጨባጭ ሁኔታ አገናዝበን፣ ዘላቂ የነገን ህይወት እንድንገነባ ያስችለናል፡፡ ሀገራችን በትውልድ ቅብብሎሽ እኛ ጋር ደርሳለች፡፡ አሁን እኛ አደራ ተሸካሚዎች ነን፡፡
ከትናንቱ ትውልድ ሀገር የሚያሻግሩና የሚያሰባስቡንን ትርክቶች እንውረስ፡፡
ለጊዜያዊ ጥቅም ሳይሆን፣ ለነገው ትውልድና ለዘላቄታው እናስብ፡፡
በየዘመናቱ ሀገር ለማሻገር ዘላቂ ተቋማትን የመገንባት ትልሞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በውጭ ጫና እና በውስጥ ችግሮች የተነሳ እየጎተቱን ጠንካራ ማህበራዊ እና ህጋዊ ሥርዓቶችን መዘርጋት ተስኖን እስከ ዛሬ የቤት ሥራ ሆኖብን እየታገልን እንገኛለን፡፡
ይህ ደግሞ በየጊዜው ለሚመጡ ፈተናዎች ጊዜያዊ መፍትሄ ላይ እንድናተኩር እና ቀልባችንን ሰብሰብ አድርገን ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ እንዳናደርግ አድርጎናል፡፡
በሌላ መልኩ ድህነታችን ስለ ነገ ከማሰብ ይልቅ ለዕለት ጉሮሯችን ብቻ እንድንጨነቅ ሲያደርገን ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋጋሚ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እያስተናገድን በየጊዜው አለመረጋጋት ውስጥ እንድንቆይ አስገድዶናል፡፡
እናማ አሁን ያ ጊዜ ሊያልፍ እና ልንነቃ ይገባናል! ሀገራችንን መጠበቅ የእኛ የአሁኖቹ ትውልድ ድርሻ ነውና፡፡ አንድነታችንን፣ ሰላማችንን፣ ሉዓላዊነታችንን እና ደህንነታችንን የማስከበር ኃላፊነት አለብን፡፡ እነዚህን ማስከበር የፀጥታው አካል ስራ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛ የዜጎች የእያንዳንዳችን የዕለት ተዕለት ተግባር እና ግዴታ መሆን አለበት፡፡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፏችንን እንዳሳየነው ሁሉ፣ በሀገራችን ጉዳዮች በንቃት ስንሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ አደጋዎችን በቀላሉ መቋቋም ትችላለች።
ታዲያ እኛ እንደ ህዝብ ምን እናድርግ?
• ሀገራችንን እንጠብቅ! ሀገር መጠበቅ የመንግሥት የሥራ ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ለደህንነታችን ዘብ እንቁም፡፡ የአካባቢያችንን ሰላም በጋራ መጠበቅ እና አጠራጣሪ ድርጊቶችን ለህግ አስከባሪዎች በፍጥነት ማሳወቅ ይገባናል፡፡ ይህ የዜግነት ግዴታችንም ነው፡፡
• አንድነታችንን እናጠናክር! ለከፋፋይ አስተሳሰቦች ጆሮ አንስጥ፡፡ ማህበራዊ ትስስራችንን የሚያላሉ የጥላቻ ንግግሮችን እና የህዝብ ለህዝብ ግጭቶችን መከላከል አለብን። አንዳችን ለሌላችን ጋሻ ነን፡፡ የተለየ አስተሳሰብ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሊኖረን ይችላል፡፡ ይህ ውበት እንጂ የሚያራርቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመከባበር ለመኖር፣ የሀገርን ሰላም የሚነሱ ዋልታ ረገጥ ትርክቶችን እንከላከል፤ ማህበራዊ አንድነታችንን እናረጋግጥ፡፡ ያኔ ጠላቶቻችንም መግቢያ ቀዳዳ ያጣሉ፤ እኛም ሰላም እንሆናለን፡፡
• ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን እንዋጋ! በየመስካችን በታማኝነት እንሥራ! እኛም ህጋዊ አሰራሮችን ብቻ እንከተል፡፡ ግብራችንንም በታማኝነት እንክፈል፡፡ ህግን አክብረን እናስከብር፡፡
• በራሳችን ምርት እንኩራ! የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም እና ኮንትሮባንድን በመከላከል የሀገር ኢኮኖሚን ከውድቀት እንጠብቅ።
• የህዝብ መሠረተ ልማቶችን ከውድመት እንከላከል፡፡ የልማት ተቋማትን እንንከባከብ፡፡ ዛሬ የእኛ ናቸው፣ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ነገ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ይሻገራሉ፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ወረት እናቆይ፡፡
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!