አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሱዳን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሱዳናውያን መሪነትና ባለቤትነት የሚመራ አካታች የፖለቲካ ሂደት ለመፍጠር ሙሉ ቁርጠኞች ነን አሉ አምስቱ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት።
የአፍሪካ ሕብረት፣ ኢጋድ፣ የዓረብ ሊግ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በአዲስ አበባ ከተማ ከሱዳን የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂዱት የነበረው የምክክር መድረክ መጠናቀቁን አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ተቋማቱ በመግለጫቸው የምክክር መድረክ ባለፈው ሚያዚያ ወር በበርሊን የተካሄደው የሰላም ጉባኤ ቀጣይ ክፍል መሆኑን ገልጸው÷ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የሱዳን የፖለቲካ እና የሲቪል ማህበረሰብ አካላት መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
የምክክሩ ዋና ዓላማ ሁሉንም የሱዳን ወገኖች ሊያሳትፍ ለሚችለው “የሱዳናውያን የእርስ በርስ የፖለቲካ ውይይት” አዘጋጅ ኮሚቴ የሚቋቋምበትን አመቺ መንገድ ለመቀየስ መሆኑ ተገልጿል።
ሱዳን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የፖለቲካ፣ ሰብዓዊ እና የደህንነት ቀውሶች ውስጥ የምትገኝ ሲሆን÷ የአዲስ አበባው ምክክር በሲቪልና ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል እምነትን ለመገንባትና ውይይትን ለማበረታታት እንደሚረዳ ተጠቁሟል።
እንዲሁም የሀገሪቱን ችግር ስርነቀል በሆነ መንገድ ሊፈታ የሚችል ተዓማኒነት ያለው አካታች የፖለቲካ ሂደት ለመመስረት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተመልክቷል።
በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተወጣጡ የሱዳን ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን የሰነድ ረቂቆች ማዘጋጀታቸውና የጽሑፍ እቅዶቻቸውን ለአምስቱ ተቋማት ማስረከባቸው ተጠቁሟል።
ይህም ወደፊት ሰፊ የሱዳን ድምጾችን ላካተቱ ጠንካራ ውይይቶች አስተማማኝ መሰረት የጣለ መሆኑን ተቋማቱ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
በመጨረሻም የሱዳንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያከብሩ በማረጋገጥ የሀገሪቱን መንግሥታዊ መዋቅር የሚከፋፍሉ ማናቸውንም ጥረቶች ውድቅ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አካላት በሙሉ በሱዳን ያለውን ውጥረት ለማርገብና ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት