የሀገር ውስጥ ዜና

ከሉዓላዊነት ወደ ዓለም…

By Melaku Gedif

June 09, 2026

የኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን ግብርናችንን ከባህላዊ የማረሻ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመሸጋገር ላይ ይገኛል።

ይህም የግብርና ሥራችን ከዝናብ ጥገኝነት እንዲወጣ ከማድረግ አንጻር አስተዋጽዖው ከፍተኛ ነው፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን እመርታ ግብርናውን በመስኖ አጠቃቀም በመደገፍ በዓመት ቢያንስ ሁለትና ሦስት ጊዜ ማምረት አስችሏል።

የአርሶ አደሩን ምርት ለዕለት ጉርስ ብቻ ከመሆን አውጥቶ ጥራቱን የጠበቀና ለዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ወደ ማዘጋጀት አሸጋግሯል፡፡

ይህ የግብርና ሽግግር ምርትን ከራስ ፍጆታ ወደ ገበያ አቅርቦት እያሳደገው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን ጉዞ ከባህላዊ የሰውና የከብት ጉልበት ወደ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለመሸጋገር ሰፊ የፖሊሲ ለውጦች እና የመሠረተ-ልማት ስርጭቶች እያደረገ ይገኛል። በተለይም በቅርቡ የወጣው የአስር ዓመቱ ብሔራዊ የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ (ከ2018-2027 ዓ.ም / 2026-2035 G.C) ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መሪ ዕቅድ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት ዓለም ከደረሰበት የግብርና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ደረጃ ለመደርስ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በግብርና ሥራ ውስጥ ለማስረጽ እየተሠራ ነው፡፡

ይህም ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር ሚናው ከፍተኛ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በአማካይ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ የእርሻ መሬት በአሁኑ ወቅት በከፊልም ቢሆን በማሽነሪ ታግዞ ይታረሳል።

ይህም አነስተኛ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በጋራ በማገናኘት በትላልቅ ማሽነሪዎች በኩታ ገጠም እንዲጠቀሙ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።

መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች እና ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎች ያለቀረጥ ወደ ሀገር እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡ ይህ ደግሞ የግብርናውን የሽግግር ጅማሮ አፋጥኖታል።

ነዳጅ ለሌላት ኢትዮጵያ፣ በምግብ ራስን መቻል የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ካለን ኃብት አንጻር ደግሞ የግብርናውን ሽግግር በማፋጠን እና የገበያውን ጉድለት በመሙላት ዓለምን መመገብ እንችላለን፡፡

ለዚህ ደግሞ በስንዴ ልማት የተመዘገበው የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ፣ የጅማሯችን ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡

መንግሥት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርት ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ርሶአደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን እንዲያገኙ በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት አበክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡

አርሶአደሮች በቁጠባና በብድር መልክ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን የሚያገኙበትን አማራጭ አመቻችቷል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት አሰጣጡ ከባህላዊ አሰራር ይልቅ በአንድ ሄክታር መሬት የሚገኘውን ምርታማነት ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡

የአርሶአደሩን ድካም፣ ጊዜ እና የምርት ብክነት በመቀነስ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት የሚቻለው የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ያሉ ሲሆን፣ በዚህም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለአብነት ይጠቀሳል፡፡

የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን እንዲገጣጥሙ፣ በሂደትም ወደ ማምረት እንዲገቡ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዘርፉን ለመደገፍ የግብርና ሜካናይዜሽን ፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍ አጋርነት በማሳደግ፣ በሀገር ውስጥ በዲጂታል እና የፋይናንስ ትስስር ከግል የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በመተባበር ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን ኪራይና የፋይናንስ ብድር አቅርቦት ተመቻችቷል፡፡

ማምረትና መገጣጠምን በመደገፍ እና የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

የኩታ ገጠም እርሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱም ለግብርና ሜካናይዜሽን መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በመደረጉ የአርሶአደሩ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም እያደገ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

ለአብነትም በ2012 ዓ.ም 1 ሺህ 316 የነበረውን የትራክተር ቁጥር ወደ 27 ሺህ እንዲሁም የኮምባይነር ቁጥር ከ448 ወደ 8000 ማድረስ ተችሏል፡፡

ኑ፤ ሀገር እንሥራ!