የሀገር ውስጥ ዜና

የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ከ2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲቀርብ ተወሰነ

By abel neway

June 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 2 ትሪሊየን 339 ቢሊየን 268 ሚሊየን 126 ሺህ 738 ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተወስኗል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል 2 ትሪሊየን 339 ቢሊየን 268 ሚሊየን 126 ሺህ 738 በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ረቂቅ በጀቱ የቀረበው የ2019 የፌዴራል መንግሥት በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው የ2019 – 2021 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና የመካከለኛ ዘመን (2019 – 2023) የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና አላማዎች እንዲሁም በመንግሥት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ኃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም ተዘጋጅቶ መቅረቡ ተመላክቷል።

ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።