አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂ መፍትሄ ያልተገኘለት የእስራኤልና ኢራን ጦርነት አሁንም የቀጣናው ብሎም የዓለም ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ሁለቱ ባላንጣ ሀገራት ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የቀጣናው ውጥረት ጋብ ብሎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በትናንትናው ዕለት በሀገራቱ መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት የአካባቢውን ውጥረት በድጋሚ እንዳያንረው ተሰግቶ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
በጥቃቱ ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት የፈጸመች ሲሆን÷ በተመሳሳይ እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ አጸፋዊ ርምጃ ወስዳለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ÷የእስራኤል እና ኢራን ግጭት እንደአዲስ በመቀስቀሱ ሀገራቱ አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም እስራኤል እና ኢራን የተኩስ አቁሙ በድጋሚ ካልተጣሰ በስተቀር ምንም አይነት ጥቃት እንደማይፈጽሙ አስታውቀዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ÷ በኢራን ላይ የሚፈጸመው የአየር ጥቃት ለጊዜው መቆሙን አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከኢራን እና ሂዝቦላህ ጋር ያለው የቤት ሥራ አለመቋጨቱን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የኢራን ጦር በበኩሉ ÷ ቴህራን በእስራኤል ላይ የምትፈጽመውን የትኛውንም ጥቃት ማቆሟን ይፋ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል እስራኤል እና ኢራን አንዱ ወገን የተኩስ አቁሙን የሚጥስ ከሆነ አንዳቸው በሌላኛው ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንደሚያጠናክሩ አስገንዝበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሀገራቱ መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት መቆሙን አድንቀው ÷በአሜሪካና ኢራን መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚኝ ጠቁመዋል፡፡
የድርድሩ ውጤቱ ለሁሉም ወገን ጠቃሚ ይሆናል ማለታቸውም ነው የተገለጸው፡፡