የሀገር ውስጥ ዜና

በክረምት ሊኖር የሚችልን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው

By Melaku Gedif

June 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪው ክረምት ሊኖር የሚችልን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡

በአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ሥራ አስፈፃሚ ገበየሁ ሊካሳ (ዶ/ር) ÷ አገልግሎቱ ለኃይል መቆራረጡ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በጥናት መለየቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ያረጁ መስመሮችን የመተካት፣ አቅምን የማሳደግና በዋናው ግሪድና በፀሐይ ኃይል አማራጮች አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ሥራዎችን በከፍተኛ ወጪ እያከናወነ ነው ብለዋል።

የኃይል መቋረጥ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች እንደሚከሰት ጠቁመው÷ የመጀመሪያው ለጥገና፣ ለአዳዲስ ትራንስፎርመሮች ተከላና መስመር ለማዛወር ሲባል በዕቅድ የሚቋረጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

2ኛው ደግሞ በእርጅና ወይም በአደጋ ምክንያት የምሶሶዎች መውደቅ፣ የመስመሮች መበጠስና የኢንሱሌተሮች መፈንዳት የሚያስከትሉት ድንገተኛና ያልታቀደ ብልሽት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ እስካሁን በተከናወኑ የቅድመ መከላከል ሥራዎች በአዲስ አበባ 1 ሺህ 750 ኪ.ሜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ 62 ሺህ 274 ኪ.ሜ የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር ፍተሻ ተደርጓል ነው ያሉት።

በ67 ሺህ 131 ትራንስፎርመሮች ላይ በተደረገ ምርመራም በዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ ላይ ከተገኙት ችግሮች 92 በመቶውን፣ በትራንስፎርመሮች ላይ ደግሞ 86 በመቶውን የማስተካከል ርምጃ ተወስዷል፡፡

በዚህም በመስመር ውስጥ የገቡ ዛፎችን የማስወገድ፣ ያዘመሙና ያረጁ የእንጨት ምሶሶዎችን እንዲሁም ኢንሱሌተሮችን የመቀየር ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በመሰረተ ልማት ማስፋፋትና አቅም ማሳደግ ረገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 99 ኪ.ሜ የመካከለኛና ዝቅተኛ መስመር መልሶ ግንባታ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

በ1 ሺህ 579 ነባር ትራንስፎርመሮች ላይ የአቅም ማሻሻያ ተደርጓል ያሉት ሥራ አስፈፃሚው÷ በከፍተኛ ጭነት ምክንያት የሚቋረጡ መስመሮችን ለመቀነስ ከ53 በላይ መጋቢ መስመሮችን የማመጣጠን ሥራ ተከውኗል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ተጀምረው የነበሩት የሀረር፣ ወላይታ፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

የ10 ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ መልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሒደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

በእነዚህ ሥራዎች አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም በአማካኝ 27 ጊዜ የነበረው የወርሃዊ የሃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ በየካቲት ወር ወደ 15 ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡

የኃይል መቋረጥ የቆይታ ጊዜም በ2017 ዓ.ም ግንቦት ወር ከነበረበት 24 ነጥበ 9 ሰዓት በ2018 ዓ.ም ግንቦት ወር ወደ 14 ነጥብ 6 ሰዓት ዝቅ ማለቱን ነው ያስረዱት፡፡

መጪውን የክረምት ወቅት ተከትሎ ሕብረተሰቡ በአንጻራዊነት የተሻለ የኃይል አቅርቦት እንዲኖረው ለማድርግም በአሁኑ ወቅት በሰፊው እየተከናወኑ ያሉና በዕቅድ የሚቋረጡ የፕሮጀክት ሥራዎችን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰተራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡