የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በ43 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው

By Melaku Gedif

June 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በ43 ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተካሄደ ነው አለ የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ 43 ከተሞች ውስጥ ማዘጋጃ ቤቶችን ጨምሮ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።

በኮሪደር ልማት የክልሉ ከተሞች ከጎስቋላ ገፅታ ተላቀው ምቹ የሥራ፣ የመኖሪያና የቱሪዝም መዳረሻ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

የወልድያ ከተማን የኮሪደር ልማት መመልከታቸውን ጠቁመው÷ ሥራው በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ አስደናቂ ሒደት ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ከከተማ ውበት እና ገጽታ ባለፈ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታን እያስገኘ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሌሎች ከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡